የሀገር ውስጥ ዜና

1 ሚሊየን ብር ጉቦ ሲቀበል ተገኝቷል የተባለው የጉሙሩክ አስተላላፊ ተከሠሠ

By Alemayehu Geremew

December 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 1 ሚሊየን ብር ጉቦ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ ተይዟል በተባለው የጉምሩክ ትራንዚስተር (አስተላላፊ) ላይ የሙስና ወንጀል ክሥ ተመሰረተ።

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሹ የጉምሩክ ትራንዚስተር (አስተላላፊ) ግዑሽ አዳነ አበራ እንደሚባልም ተመላክቷል፡፡

የፍትኅ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬቶሬት ዐቃቢ-ሕግ ተከሳሹን የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 27 ሥር የተደነገገውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት በተከሳሹ ላይ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦበታል።

በዚህም ባቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ በሚሰራው የጉምሩክ አስተላላፊነት ስራ መሰረት ከቀረጥ ነጻ ለኢንቨስትመንት የገባን “ቶዮታ ሀይሉክስ” ተሽከርካሪ ÷ ነብዩ ቡሽራ ጅማ ከተባለ የግል ተበዳይና 1ኛ የዓቃቢ ሕግ ምስክር ከሆነው ግለሰብ ጋር በመሆን የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ለመፈፀም በመስማማት የግል ተበዳይን የሰባት ዓመት የመኪናውን ቀረጥ እና ታክስ 1ሚሊየን 511 ሺህ 356 ከ66 ሣንቲም እንዲከፍሉና ተሸከርካሪውን በአካል እንዲያቀርቡ መናገሩን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።

ከዚህም በኃላ የግል ተበዳይ በኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ/ም ልዩ ቦታው ሳሪስ አቦ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው የጉምሩክ ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ሲቀርቡ ተከሳሹ ተሽከርካሪው ለጥያቄ እንደሚፈለግ እና መሿለኪያ ኃይሌ ይርጋ ሕንጻ ላይ በሚገኘው የጉምሩክ ዋና መሥሪያ ቤት መጠየቅ እንዳለባቸው መግለጹም ተጠቅሶ በክሱ ዝርዝር ተካቷል።

በዚህ መልኩ ተሽከርካሪው እንዲለቀቅ ከጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር እንደሚያደራድራቸው ለግል ተበዳይ በመንገር እና መኪናውን ለመልቀቅ የግል ተበዳይ 1 ሚሊየን ብር እንዲከፍሉ ኃላፊዎች መግለፃቸውን በማሳወቅ በኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ/ም በግምት ከቀኑ 7 ሠዓት ከ30 አካባቢ ቦሌ መድሃኒያለም አከባቢ ልዩ ቦታው ኦኬዥን ካፌ ውስጥ ከግል ተበዳይ ጋር በመገናኘት 1 ሚሊየን ብር በአቢሲኒያ ባንክ የተጻፈ ቼክ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በክሱ ተጠቅሶ ዐቃቢህግ የማቀባበል የሙስና ወንጀልክስ አቅርቦበታል።

ዐቃቤ ሕግ ከክስ ዝርዝሩ ጋር የሰውና የሠነድ ማስረጃ አያይዞ አቅርቧል።

ተከሳሹ ችሎት ቀርቦ ክሱ እንዲደርሰው ከተደረገ በኋላ የክስ ዝርዝሩ በችሎት በንባብ ተሰምቷል።

በታሪክ አዱኛ