ቴክ

ለኢትዮጵያን እድገት በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ወሳኝ ነው ተባለ

By Meseret Awoke

December 26, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን እድገት ለማፋጠን በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ ያለውን አቅም አሟጦ መጠቀም ወሳኝ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሕንድ ከሚገኙት ከጄኤስ ዩኒቨርሲቲ እና ካላላ ላንግዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዞን የማጎልበት እና የባለ ድርሻ አካላትን አቅም የመገንባት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመቅዳትና በማላመድ በዘርፉ ያለውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገቷ ለማጎልበት በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ከሁሉም የትብብር አካላት ጋር በትኩረት መሰራት እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቴክኖሎጂ ሽግግር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችንና ዩኒቨርሲቲዎችን ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው ፥ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ዩኒቨስርሲቲዎች ጋርም እየሰራች መሆኑን አብራርተዋል።

በዘርፉ ከዚህ በፊት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን የሚገመግም፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና የመስጠት እና ቀጣይ አቅጣጮዎችን የመለየት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡

በአቅም ግንባታ ስልጠናው ከኢንዱስትሪዎች፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ከሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፍ የተውጣጡ እየተሳተፉ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡

ስልጠናውም በቴክኖሎጂ ማላመድና ሽግግር፣ በኢንዱስትሪ እና በማምረቻ ተቋማት ቴክኖሎጂን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተሞክሮዎች፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና የአመራር ዘዴ ዙሪያ ያተኮረ ነው፡፡