Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢራን አብዮታዊ ዘብ የጦር አማካሪ መገደላቸው ተሰማ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢራን አብዮታዊ ዘብ የጦር አማካሪ ዚያድ ራሲ ሙሴቪ በእስራዔል ተፈጽሟል በተባለ የአየር ጥቃት በሶሪያ መገደላቸውን የሀገሪቱ ቴሌቪዝን አስታውቋል፡፡

ፕሬስ ቴቪ እንደዘገበው የጦር አማካሪው በሶሪያ ደማስቆ አቅራቢያ በምትገኘው ሳይዳ ዜይናብ ከተማ በሶሪያ እና በኢራን መካከል ያሉትን ወታደራዊ ጉዳዮች እያስተባበሩ ባሉበት ወቅት በእስራኤል በተፈፀመ የአየር ጥቃት ህይወታቸው አልፏል፡፡

የጦር አማካሪው ከአራት አመት በፊት በአሜሪካ የተገደሉት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ሌተናል ጀነራል ቃሲም ሱሌይማኒ የስራ አጋር እንደነበሩ ተመላክቷል፡፡

እንደ ዘገባው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ የአማካሪው ህልፈት እንዳስቆጣውና አፀፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝቷል፡፡

በጉዳዩ ላይ ለመላው ኢራናውያን ዝርዝር መግለጫ እንደሚሰጠም አብዮታዊ ዘቡ ገልጿል ነው የተባለው።

የእስራኤል መንግስት በሶሪያ የኢራን ይዞታዎች ናቸው ባላቸው ወታደራዊ ቦታዎች ላይ ለዓመታት ጥቃት ሲፈፀም መቆየቱን ፕሬስ ቲቪ እና አልጀዚራ ዘግበዋል።

Exit mobile version