Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በመዲናዋ ለገና በዓል ግብዓቶችን የሚያቀርቡ አውደ ርዕይዎች ሊከፈቱ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሳምንቱን ሙሉ የተለያዩ ግብአቶችን የሚያቀርቡ አውደ ርዕይዎች ሊከፈቱ መሆኑን የከተማዋ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ አውደ ርዕይዎቹ በመዲናዋ በተመረጡ ቦታዎች ይከፈታሉ።

አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ለበዓል ተፈላጊ የሆኑ ግብአቶች በአውደ ርዕይዎቹ እንደሚቀርቡም ነው አቶ ሰውነት የገለጹት።

የበዓል አውደ ርዕይዎቹ ሳር ቤት፣ መገናኛ፣ ስድስት ኪሎ እና መሰል ቦታዎች ላይ እንደሚከፈቱ ተገልጿል፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ አምራች እና አቅራቢዎች በአውደ ርዕይዎቹ እንደሚሳተፉባቸውም ተመላክቷል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ነጋዴዎች በቅዳሜ እና እሁድ ገበያ ከመደበኛው የገበያ ዋጋ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቀንሰው እንዲሸጡ ስምምነት ላይ መደረሱን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ አስታውቀዋል፡፡

የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይም ጠንካራ ቁጥጥር እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህን ተከትሎም ከ10 ሺህ በላይ ሕገ-ወጥ ንግድ በፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

በዙፋን ካሳሁንና አልማዝ መኮንን

Exit mobile version