Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ስለመንፈስ ጭንቀት ምን ያህል ያውቃሉ?

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንፈስ ጭንቀት በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል የአዕምሮ መታወክ ችግር ነው፡፡

ጭንቀት ለማሳካት የምንፈልጋቸው ነገሮች ከዓቅም በላይ ሲያሳስቡን እና ስናውጠነጥን የሚፈጠር ከገደብ ያለፈ ስሜት ነው፡፡

የመንፈስ ጭንቀት ከሚያሳያቸው የተለመዱ ምልክቶች መካከል ፦ እረፍት አልባነት፣ ከልክ ያለፈ ጭንቀት፣ ብስጭት፣ ትኩረት ለማድረግ መቸገር እና እንቅልፍ ማጣት ይጠቀሳሉ፡፡

በተጨማሪም ÷ የፀጉር መነቃቀል እና መመለጥ፣ የእንቅልፍ እጦት፣ ራስ ምታት፣ መነጫነጭ ፣ መደበት እና እንደመንቀጥቀጥ ማላብ ያሉ የባህሪ ለውጦች ሊያስከትል ይችላል፡፡

ጭንቀት ከፍላጎቶች ወይም ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማጣጣም ሲከብድ የሚፈጠር ስሜት ነውም ሊባል ይችላል፡፡

አንድ ሰው ጭንቀቱን መቆጣጠር ሲከብደው ሥር ወደሰደደ ሕመም ሊያመራ እንደሚችል የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ውጥረት የበዛበት የሥራ ሁኔታ እና ከባቢ፣ ሰዎች ከሰዎች ጋር የሚኖራቸው ያልተመቸ ግንኙነት እና መስተጋብር ፣ ከኢኮኖሚ እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አጣብቂኝ ሁኔታዎች እና የመሳሰሉት ጭንቀት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

ጭንቀት ለደም ግፊት መጨመር፣ ለልብ ሕመም፣ በጡንቻዎች ላይ ለሚፈጠር የሕመም ስሜት፣ ለወገብ እና ጀርባ ሕመም ፣ ለአስም ህመም፣ ለጨጓራ ሕመም እንዲሁም ለአንጀት ቁስለትም መንሥዔ ሊሆን እንደሚችልም የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ መሥራት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን መመገብ እና በሽታ የመከላከል ዐቅም መገንባት፣ የሚወሰዱ የአልኮል መጠጦች እና አነቃቂዎችን እንዲሁም የተለያዩ መድሐኒቶችን መቀነስ ከጭንቀት ለመውጣት አስቻይ መንገዶች እንደሆኑም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

የተለያዩ የኤሮቢክስ ስፖርቶችን ማዘውተር፣ መዝናናትና መዋኘትም ጭንቀትን ለማስወገድ ሚናቸው ቀላል አለመሆኑን ሜዲካል ኒውስ ቱደይ በመረጃው አንስቷል፡፡

የአንድ ሰው ጭንቀት ከላይ በተጠቀሱት የመፍትሄ ሃሳቦች የማይመለስ ከሆነና ሥር ከሰደደ ሐኪም ዘንድ በመቅረብ እና በማማከር ለችግሩ መፍትሄ የሚያገኝበት መንገድ እንዳለም ተነግሯል፡፡

Exit mobile version