የሀገር ውስጥ ዜና

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈጻጸም 62 በመቶ መድረሱን አስታወቁ

By Amele Demsew

December 22, 2023

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 12 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈጻጸም 62 በመቶ መድረሱን አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግምገማ አድርገዋል።

በዚህም “ከ2013 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ለ12ኛ ጊዜ ባካሄድኩት የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግምገማ በለወጥነው የፕሮጀክት አስተዳደር እና ክትትል ስርዓት የተነሳ የአጠቃላይ ግንባታው ሂደት 62 በመቶ መድረሱን በመመልከቴ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአፍሪካ ደረጃ በግዙፍነታቸው አንደኛ እና ሶስተኛ የሆኑት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ እና የኮይሻ ግድቦች ባለቤት በመሆናችን የንፁህ የኃይል ማመንጨት ስራችንን እና ጥረታችንን አቻ የሌለው ያደርገዋል” ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፡፡

በቅርብ ርቀት በጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅን በምንመርቅበት በአሁኑ ወቅት የኮይሻ ግድብ ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድል ተጨማሪ አስተዋፅኦ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡