Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሃውቲ አማፂያን በንግድ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጥምረቱ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀይ ባህር ደህንነትን ለመጠበቅ የተቋቋመው ወታደራዊ ጥምረት የሃውቲ አማፂያን በቀይ ባህር በንግድ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የሀውቲ አማፂያን በእስራኤል – ሃማስ ጦርነት ለፍልስጤማውያን ድጋፋቸውን ለማሳየት በቀይ ባህር በሚቀዝፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ሲሆን ይህን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ይህን የአማፂያኑን ጥቃት ለመከላከልም አሜሪካ መራሽ ወታደራዊ ጥምረት የተቋቋመ ሲሆን፥ አሁን ላይ ጥምረቱን የሚቀላቀሉት ሀገራት ቁጥር ከፍ እያለ ይገኛል።

የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጄኔራል ፓት ራይደር፥ “የዓለም ሀገራት የኢኮኖሚ መናኸሪያ በሆነው የቀይ ባህር መስመር አማፂያኑ የሽፍትነት ተግባር እየፈፀሙ ይገኛል” ብለዋል፡፡

ወታደራዊ ጥምረቱ ቀይ ባህርን እና የኤደን ባህረ ሰላጤን እየጠበቀ ይገኛል ያሉት ቃል አቀባዩ፥ሃውቲዎች ለሚፈፅሙት ጥቃት ምላሽ ለመስጥት ጥምረቱ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሰሜናዊ የመን የሚገኙ የሃውቲ አማፂያን በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት እንዲያቆሙም ቃል አቀባዩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እስራዔል በጋዛ እየወሰደች ያለው ወታደራዊ ዘመቻ የባህረ ሰላጤውን ሀገራት ማስቆጣቱ የተገለፀ  ሲሆን አማፂያኑን ጨምሮ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ለእስራዔል ወታደራዊ ምላሽ ለመስጠት እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው መባሉን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version