የሀገር ውስጥ ዜና

በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው ልዑክ ከሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ጋር ተወያየ

By Amele Demsew

December 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራው የልዑካን ቡድን ከቻይናዋ ሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ዙ ሹንዚው ጋር ተወያይቷል::

ከንቲባ አዳነች በወቅቱ እንዳሉት÷ የሱቿን ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ቼንዱ ከተማ የ”ፓርክ ከተማ” ጽንሰ-ሀሳብ እና የአረንጓዴ ከተማ ስርዓት ግንባታ የሚደነቅ ነው፡፡

ቼንዱ ከተማ የከተማ ልማትን ከፓርክ ጋር በማስማማት ለከተሞች አዳዲስ ገጽታ በመፍጠር ረገድ መልካም ተሞክሮ ያላት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ትገኛለች ያሉት ከንቲባዋ÷ የቻይና ቱሪስቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ በቀጣይ ኢትዮጵያን ለቻይና ጎብኚዎች ተመራጭ መዳረሻ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለንም ብለዋል።

የሱቿን ግዛት ኮንግረስ ምክትል ሰብሳቢ ዙ ሹንዚው በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት በማንኛውም ሁኔታ ፀንቶ ወደ ሚቆይ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት አድጓል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በገቢና ወጪ ንግድ፣ በቱሪዝም፣ በቴክኒክ ሙያ ትምህርት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ በትብብር ለመስራት የእህትማማችነት ስምምነት ለመፈራረም እንደሚፈልጉ ምክትል ሰብሳቢዋ ገልፀዋል::