ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአሜሪካና የቻይና ወታደራዊ ባለስልጣናት ከዓመት በኋላ የመጀመሪያ ውይይት አደረጉ

By Tamrat Bishaw

December 22, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከአንድ ዓመት በላይ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ውይይታቸውን አድርገዋል፡፡

የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ከቻይና አቻቸው ጋር የቪዲዮ ስብሰባ ማድረጋቸውን ፔንታጎን ገልጿል፡፡

ቤጂንግ እንዲህ ዓይነቱን ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ንግግሮች ያቆመችው የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ በፈረንጆቹ 2022 መሐሴ ወር ላይ በራሳቸው ተመርተው ታይዋንን ከጎበኙ በኋላ መሆኑን ገልፃለች።

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ወር ሲገናኙ ውይይታቸውን ለመቀጠል ተስማምተው እንደነበር ተመላክቷል።

የአሜሪካ የአየር ኃይል ጀነራል ቻርልስ ኪው ብራውን፣ የጋራ የጦር አለቆች ሊቀ መንበር እና የቻይና ህዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር ጄኔራል ሊዩ ዠንሊ በርካታ ዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ የደህንነት ጉዳዮችን አንስተው እንደተወያዩ የአየር ሃይሉ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ አስታወቋል።

አሜሪካ እና ቻይና ጤናማ፣ የተረጋጋ እና ቀጣይነት ያለው ወታደራዊ-ለወታደራዊ ግንኙነት ለመፍጠር ቁልፉ ጉዳይ አሜሪካ ስለ ቻይና ትክክለኛ ግንዛቤ መያዝ ነው ሲል የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ሐሙስ እለት መግለጫ ማውጣቱን ሊዩ ጠቅሰዋል።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከቻይና አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በካሊፎርኒያ ህዳር ወር ላይ ተገናኝተው ውጥረቱን ለማርገብ በሚደረገው ጥረት ወታደራዊ-ለወታደራዊ ግንኙነቶችን ወደ ነበረበት ለመመለስ ተስማምተዋል።

በውይይቱ ወቅት ሊዩ አሜሪካ የቻይናን የግዛት ሉዓላዊነት እና በደቡብ ቻይና ባህር ላይ ሰፊ የባህር ላይ መብቶችን እና ጥቅሞችን እንድታከብር ጠይቀዋል።