አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከከተሞቻችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ በላቀ ትጋት ማገልገላችንን እንቀጥላለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመራ ልዑክ በቻይና የተለያዩ ከተሞች የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው፡፡
ልዑኩ ሻንጋይን ከጎበኘ በኋላም ከከተማዋ ከንቲባ ጎንግ ዜንግ ጋር መምከሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
ውይይቱን ተከትሎም በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱንም ገልጸዋል፡፡
የሻንጋይ ከተማን የትራንስፖርት ማኔጅመንት፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ የሙዚየም አገልግሎት፣ የቆሻሻ አስተዳደር ማዕከልን እና የሎጂስቲክ አገልግሎቶቻቸውን መጎብኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በጉብኝታችንም ለኢትዮጵያ ከተሞች የሚጠቅሙ ሐሳቦችንና ልምዶችን አግኝተናል ነው ያሉት፡፡
በተለይም አዲስ አበባ ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት የማድረግና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ዐቅም በመፍጠር እያስመዘገብን ያለነውን ለውጥ ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው ብለዋል፡፡