የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ከህንድ ባለሃብቶች ጋር ተወያዩ

By Amele Demsew

December 19, 2023

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 9 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ የተካሄደው በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከህንድ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የቢዝነስ ምክክር መድረክ ጎን ለጎን የተካሄደ ነው።

በውይይቱ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ እና ሌሎች የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በውይይቱ ወቅት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በክልሉ ያለውን ሰፊ የኢንቨስትመንት አቅም ለባለሃብቶቹ አስረድተዋል፡፡

ክልሉ በተፈጥሮ ሃብት በግብርና፣ ለም አፈር እና እምቅ የውሃ ሃብት የበለጸገ መሆኑን በመጥቀስ የህንድ ባለሃብቶች በክልሉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚያዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በምታደርገው የለውጥ ጉዞ የህንድ ባለሃብቶች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በጉባኤው ከ30 በላይ የህንድ ኩባንያዎች ተሳታፊ መሆናቸውን በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡