አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ምዕራብ ቻይና ትናንት ምሽት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢያንስ 116 ሰዎች ሲሞቱ 220 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል፡፡
የቻይና ባለስልጣናት እንዳሉት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 2 የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ በጋንሱ ግዛት እና በጎረቤት ኪንጋይ ላይ መከሰቱ ተሰምቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከፍተኛ ቅዝቃዜ ባለበት አካባቢ ላይ ሰዎችን ለመርዳት እየጣሩ እንዳሉም ተጠቁሟል።
ከሰዓታት በኋላ ደግሞ በሬክተር ስኬል 5 ነጥብ 5 የተመዘገበ ሁለተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ በጎረቤት ዢንጂያንግ የተከሰተ ሲሆን÷ ያደረሰው ጉዳት አለመታወቁ ተመላክቷል፡፡
የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ አደጋው ለደረሰበት የጋንሱ አካባቢ ሙሉ የነፍስ አድን ስራ እንዲሰራ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አደጋውን ተከትሎ በአካባቢው የመብራት እና የውሃ አቅርቦት በመቋረጡ በነፍስ አድን ስራው ላይ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።
ባለፈው መስከረም በደቡብ ምዕራብ ሲቹዋን ግዛት በሬክተር ስኬል 6 ነጥብ 6 በተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት ከ60 በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።