Nurse Visiting Senior Male Patient At Home

ጤና

ደም ግፊትን ያለ መድሃኒት እገዛ መቆጣጠር እንደሚቻል ያውቃሉ?

By Amele Demsew

December 19, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ደም ግፊትን የምንከላከልባቸው እና ከተከሰተ በኋላም ያለምንም መድሃኒት እገዛ መቆጣጠር የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ በዘርፉ የተጠኑ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

የደም ግፊት ማለት ልባችን ደም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለማሰራጨት ሲል በደም ቅዳ ቧምቧዎች ላይ የሚፈጥረው ግፊት ሲሆን በእያንዳንዱ የልብ ምት መቀነስና መጨመር የሚወሰን ነው፡፡

የሰው ልጅ የደም ግፊት መጠን በቀን ውስጥ ዝቅም ከፍም ሊል ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

የደም ግፊት ከሚገባው በላይ ሲጨምር የደም ቧምቧዎችን እና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ሊጎዳ የሚችል ሲሆን፥ ይህም የደም ብዛት ወይም ከፍተኛ የደም ግፊት ይባላል።

የደም ግፊት ከመጠን በላይ ሲጨምር ከፍተኛ ራስ ምታት፣ አልፎ አልፎ የእይታ ችግር፣ የድካም ስሜት፣ የደረት ህመም፣ የአተነፋፈስ መዛባት ወይም ለመተንፈስ መቸገር፣ የልብ ምት መዛባት፣ ራስን መሳት ወይም የሰውነት መስነፍ አይነት ምልክቶችን ሊመለከቱ ይችላሉ።

የደም ግፊት በሁለት ምድቦች የሚከፈል ሲሆን፥ ከሌሎች በሽታዎች ወይም መድሀኒቶች ጋር ተያይዞ የሚመጣ ከፍተኛ የደም ግፊት አንደኛው ነው።

ከአጠቃላይ ከፍተኛ የደም ግፊት ታካሚዎች መካከል አምስት በመቶ የሚሆኑ ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች በዚህ ምድብ ውስጥ እንደሚመደቡ የህክምነናባለሙያዎች ይናገራሉ።

እነዚህ ሰዎች የደም ግፊታቸውን ከፍ የሚያደርገው በሽታ ሲድን ወይም መድሀኒት ሲቋረጥ የደም ግፊታቸው ሊስተካከል ይችላል።

ሁለተኛው ደግሞ መሰረታዊ ከፍተኛ የደም ግፊት ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆኑ የከፍተኛ ይደም ግፊት ህመምተኞች በዚህ አይነት ከፍተኛ የደም ግፊት ህመም የሚጠቁ ናቸው።

የመሰረታዊ ከፍተኛ የደም ግፊት ትክክለኛ መንስኤ የማይታወቅ ሲሆን፥ አንዳንድ ነገሮች በዚህ ህመም የመያዝ እድልን ሊጨምሩ እንደሚችሉም ነው የሚነገረው።

በዘር ከፍተኛ ደም ግፊት መኖር፣ ከፍተኛ የጨው መጠን በምግብ ላይ መጠቀም፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጥ፣ በእድሜ መግፋት፣ የኩላሊት በሽታ፣ ከልክ ያለፈ ውፍረት እና የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ ለደም ግፊት መከሰት መንስኤ እንደሚሆኑም ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።

ደም ግፊትን ለመቆጣጠር ከማረጋጊያ መድሃኒት ባለፈ የአኗኗር ዘይቤን እና አመጋገብን በማስተካከል መቆጣጠር እንደሚቻል በጤናው ዘርፍ የተሰሩ በርካታ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

በዕለት ተዕለት ኑሯችን የምንከተለው የአኗኗር ዘይቤ እና የአመጋገብ ሁኔታ ደም ግፊት ከመከሰቱ በፊትም ሆነ ከተከሰተም በኋላ መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ይወስናል።

ደም ግፊት ከተከሰተ በኋላም መቆጣጠር የሚቻልባቸው መድሃኒቶች ያሉት ሲሆን በሽታውን ያለምንም መድሃኒት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚከተሉትን መንገዶች መጠቀም ይመከራል።

ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል (በዋነኝነት እንደ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ፣ የእህል ዘሮችና ለውዝ መመገብ፣ ጨውን ገበታ ላይ አለማብዛት) ፣ የሰውነት ክብደትን ማስተካከል፣ ከተለያዩ ሱሶች መቆጠብ።

በተጨማሪም ግፊት ያለባቸው ሰዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በመስራት፣ በቂ ውሃ በመጠጣት፣ ጥሩ የእንቅልፍ ጊዜ በማሳለፍ፣ ውጥረትን በመቀነስና የደም ግፊት ችግርን የሚያመጡ ተያያዥ የጤና ችግሮችን በማስወገድ ግፊቱን መቆጣጠር እንሚቻል ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

በሌላ በኩል ከፍ ያለ የደም ግፊት ችግር ያለባቸው ሰዎች ግን የተጠቀሱትን የአኗኗር ዘይቤዎች ከመከተል በተጨማሪ ከጤና ባለሙያ ጋር በመነጋገር ማረጋጊያ መድሃኒት መውሰድ እንደሚችሉ የኸልዝ ላይን መረጃ አመላክቷል፡፡