ዓለምአቀፋዊ ዜና

ቻይና ጥልቅ የባህር ውስጥ ቁፋሮ የምታካሂድ መርከብ ሙከራ ልታደርግ ነው

By Feven Bishaw

December 18, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራቻት ጥልቅ የባህር ውስጥ ቁፋሮ የምታካሂድ መርከብ የውሀ ላይ ሙከራ ልታደርግ መሆኑ ተመላከት።

ቻይና ከባህር በታች ያለውን ዘይትና ጋዝ ለመፈለግ የምታደርገውን ጥረት ለማሳደግ ቁልፍ እርምጃ በመውሰድ በባህር ወለል ላይ በጥልቀት መቆፈር እንደምትችል የተነገረላትን መርከቧን በመጪው ዓርብ ሙከራ ታካሂዳለች፡፡

መርከቧ በውሃ ውስጥ ምርምር ማድረግና ቁፋሮ ማካሄድ የምትችል መርከብ እንደሆነችም ተገልጿል።

ከባህር ጠለል በታች እስከ 11 ሺህ ሜትር ጥልቀት መቆፈር እንደምትችል የተነገረላት መረከብ÷ ወደ ወደብ ሳትመለስ ከ27 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዛ ለተከታታይ 120 ቀናት አገልግሎት መስጠት እንደምትችልም ተመላክቷል።

ሜንግዢያንግ (ህልም) የተሰኘችው መርከብ በማንኛውም ባህር ውስጥ የመጓዝ አቅም እንዳላት ተጠቁሟል።

ይሁን እንጂ የባህር ላይ ሙከራው የት አካባቢ ሊካሄድ እንደሚችል ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

ሜንግዢያንግ የመሞከር ሀሳብ የመጣው በደቡብ ቻይና ባህር ውጥረት በነገሰበትና የፊሊፒንስ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ጄ አር በሳምንቱ መጨረሻ ሀገራቸው በአጨቃጫቂው የውሀ አካል ላይ አዲስ የኃይል ፍለጋ ፕሮጄክቶችን መጀመር እንደምትችል ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡

ቻይና እና ፊሊፒንስ በደቡብ ቻይና ባህር በተደጋጋሚ የመርከብ ግጭቶች ሲካሰሱ መቆየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።