ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተሰምቷል፡፡
ፒዮንግያንግ ሚሳኤሉን ያስወነጨፈችው ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በቅርቡ ከሰሜን ኮሪያ የሚቃጣን የኒውክሌር ጥቃት መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
ባለስቲክ ሚሳኤሉ 15 ሺህ ኪሎ ሜትር ወይም 9 ሺህ 300 ማይል ርቀት የመጓዝ አቅም እንዳለው ተመላክቷል፡፡
ይህም የጃፓንን ሁሉም አካባቢዎች እና የአሜሪካን ዋና ዋና ግዛቶች ማካለል እንደሚያስችል ነው የተገለጸው፡፡
ከፒዮንግያንግ አቅራቢያ ወደ ሰሜን ምስራቅ ባህር የተወነጨፈው ሚሳኤል በደቡብ ኮሪያ ምድር 1ሺህ ኪሎ ሜትር መጓዙን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት የአሁኑ የሚሳኤል ሙከራ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን አለመረጋጋት ከማባባሱ ባለፈ ዓለም አቀፍ ክልከላዎችን የተላለፈ ነው ሲል ወንጅሏል፡፡
በደቡብ ኮሪያ እና በአሜሪካ የተጀመረውን የኒውክሌር መከላከል ዘመቻ ይበልጥ ማዘመን እና ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡
ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳኤሉን ያስወነጨፈችው የአጭር ርቀት ሚሳኤል ባስወነጨፈች በሰዓታት ልዩነት ውስጥ መሆኑንም ሬውተርስ ዘግቧል፡፡