የሀገር ውስጥ ዜና

በዋግ ኽምራ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

By Amele Demsew

December 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በድርቅ ለተጎዱ ዜጎቸ ከተለያዩ በጎ አድራጊዎች የተገኘ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ተደርጓል።

በዋግ ልማት ማኅበር የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተወካይ ዲያቆን ግርማ ታከለ÷ድጋፉ ከሀገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙ በጎ አድራጊ ወገኖች የተገኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም አማራ ባንክ 1 ሺህ 776 ኩንታል፣ ላይፍ ሴንተር 59 ኩንታል፣ መቄዶንያ 500 ኩንታል፣ ንቡረ ዕድ ቆሞስ አባ ብርሃነ ሥላሴ ብርሃኑ 66 ኩንታል እና ሌሎች አካላትም የተለያየ መጠን ያላቸው የምግብ ድጋፎች ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ምህረት መላኩ በበኩላቸው÷ እንደ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ከ180 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡

በቀጣይም ድጋፍ ለሚሹ ህፃናት፣ እናቶችና አረጋዊያን ለመደገፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሰል ድጋፎችን እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረባቸውንም የዋግ ኽምራ ኮሙኒኬሼን መረጃ ያመላክታል፡፡