የሀገር ውስጥ ዜና

የተገኙ ድሎችን በማስቀጠልና በማፅናት ልማትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ አወሉ አብዲ

By Amele Demsew

December 17, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል እና በማፅናት ልማትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አወሉ አብዲ ገለጹ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ወለንጪቲ ከተማ የሰላም እና ልማት ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡

አቶ አወሉ አብዲ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ÷ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ፣ የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል እና በማፅናት ልማትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም በክልሉ ተጨባጭ ለውጥ ተመዝግቧል ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ።

አሸባሪው ሸኔ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የዜጎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ በመጣል ሰላምን እያወከ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ በመንግስት የተዘረጋለትን የሰላም እጅ፥ የሕዝብ ፍላጎት ያልሆኑ ነጥቦችን በመምዘዝ እንዲሁም ከሕገ መንግስቱ በተጻረረ መልኩ በመቆም ማደናቀፉን ቀጥሏል ነው ያሉት አቶ አወሉ፡፡

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን እያከናወነ ያለውን ሕግን የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ባለፉት ዓመታት በእኩይ ተግባሮቹ ከሕዝብ ፍላጎት ተቃርኖ የቆመና የሕዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር እንዳሳየም በመድረኩ ተገልጿል፡፡

አሸባሪው ሸኔ የኦሮሞን አርሶ አደር እና እናቶችን እየበደለና እያስለቀሰ የሚያመጣው ነፃነት ፈፅሞ አይኖርም ሲሉም በኮንፈረንሱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው፥ የአሸባሪው ሸኔ ቡድን ከእኩይ ድርጊቱ እንዲታቀብ እና የሰላም አማራጮችን ሊቀበል እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሁን ላይ በአካባቢው ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረው የፀጥታ ችግር በሕዝብ እና በመንግስት ትብብር መፈታቱ ተመላክቷል፡፡

በመራኦል ከድር