Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አሜሪካና ብሪታንያ 15 የሃውቲ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትተው ጣሉ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ እና ብሪታንያ 15 የሃውቲ አማጺያን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በቀይ ባሕር መትተው መጣላቸውን አስታወቁ፡፡

የየመን ሃውቲ አማጺያን በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ እና ኮንቴነር በሚያጓጉዙ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ሃውቲ በቀጣናው የሚፈጽመው ጥቃትም ለዓለም አቀፉ ንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሃውቲ አማጺያን በተለይም ለእስራኤል የሎጂስቲክ ድጋፍ ያደርሳሉ ባሏቸው የአሜሪካ መርከቦች ላይ ኢላማ እንደሚያደረጉ ተጠቅሷል፡፡

የአሜሪካ ባሕር ሃይልም ከየመን ሃውቲ አማጺያን የተላኩ ናቸው የተባሉ 14 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን በቀይ ባሕር ላይ መትቶ እንደጣለ ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር በቀይ ባሕር ተጨማሪ አንድ የሃውቲ አማጺያን ሰው አልባ አውሮፕላን መትቶ መጣሉን ገልጿል፡፡

የሃውቲ አማጺያን በበኩላቸው÷እስራኤል በጋዛ ላይ የምታካሂደውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

Exit mobile version