የአንካራጉቹ እግርኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ፋሩክ ኮቻ ከእግር ኳስ ታገደ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጨዋታ ዳኛ በመደብደብ አስነዋሪ ተግባር የፈፀመው የቱርኩ ኤም ኬ ኢ አንካራጉቹ እግርኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ፋሩክ ኮቻ ከእግር በቋሚነት መታገዳቸውን የቱርክ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ቅዳሜ ኤም ኬ ኢ አንካራጉቹ ከችኩር ሪዘርፖር ባደረጉት ጨዋታ የእለቱ ዋና ዳኛ ሃሊል ኡሙት ሜለር ያልተገባ የቫር ውሳኔ ወስነዋል በሚል ዳኛውን በቡጢ መምታታቸው አነጋጋሪ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ጉዳዩን ሲመለከት የነበረው የቱርክ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታዎችን በጊዜያዊነት ያረዘመ ሲሆን÷በኤም ኬ ኢ አንካራጉቹ ቡድን እና በፕሬዚዳንቱ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በውሳኔው መሰረትም የኤም ኬ ኢ አንካራጉቹ እግርኳስ ቡድን ፕሬዚዳንት ፋሩክ ኮቻ በቋሚነት ከእግርኳስ መታገዱ የተገለፀ ሲሆን÷የሱፐርሊጉ ተወዳዳሪ የሆነው አንካራጉቹ 2 ሚሊየን ሊሬ ወይም የ54ሺህ ዩሮ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
በተጨማሪም ኤም ኬ ኢ አንካራጉቹ በሜዳው የሚያደርጋቸውን 5 ጨዋታዎች ያለምንም ደጋፊ እንዲጫወት ፌዴሬሽኑ ወስኗል፡፡
ከፌዴሬሽኑ ውሳኔ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ህጋዊ የጨዋታ ዳኛ በመደብደብ ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በህግ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ የቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የ37 ዓመቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኡመት ሜለር ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ በሌሎች ተጫዋቾች ድብደባ የተፈፀመበት ሲሆን ÷በተደረገለት የህክምና ክትትል በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል መባሉን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡