አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 5 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የቀጣዩ አመት ወታደራዊ ረቂቅ በጀት 886 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ሆኖ ቀረበ።
ረቂቅ በጀቱ ለዩክሬን የሚሰጥ 300 ሚሊየን ዶላር እርዳታን በተጨማሪነት ያካተተ መሆኑም ታውቋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ እና የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ (ሴኔት) ረቂቁ የአዲሱ አመት ወታደራዊ በጀት ሆኖ እንዲቀርብ በአብላጫ ድምጽ አሳልፈውታል።
ረቂቁ በኮንግረሱ 310 ለ118 እንዲሁም በሴኔቱ 87 ለ 13 በሆነ ድምጽ አብላጫ ድምጽ ጸድቋል ነው የተባለው።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንም ረቂቁ ተግባራዊ እንዲሆን በፊርማቸው ያጸድቁታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲሱ ወታደራዊ ረቂቅ በጀት የሃገሪቱን ወታደሮች ክፍያ ማሳደግን ጨምሮ ለአዳዲስ መሳሪያዎች ግዢ እንዲሁም ሰፊ ወታደራዊ ወጪዎችን ያካተተ መሆኑን የሲ ኤን ኤን እና አር ቲ ዘገባ ያመላክታል።
ከዚህ ባለፈም ካለፈው አመት የዋሺንግተን ወታደራዊ በጀት አንጻር የ3 በመቶ ጭማሪ አለውም ነው የተባለው።
የህዝብ እንደራሴዎችም ከቀረበው ረቂቅ በተጨማሪ ለእስራኤል እና ዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ የሚውል 105 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ንጥል ረቂቅ ወታደራዊ በጀትን ለማቅረብ እየመከሩ መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።
ረቂቁ ለአሜሪካ መከላከያ አባላት የ5 ነጥብ 2 በመቶ የደመወዝ ጭማሪ የሚኖረው ሲሆን፥ 168 ቢሊየን ዶላሩ ለመሳሪያ ግዢ እና ስሪት፣ 145 ቢሊየን ዶላሩ ለወታደራዊ ጥናትና ልማት እንዲሁም 32 ቢሊየን ዶላሩ ደግሞ ለሃገሪቱ የኒውክሌር ኃይል ድጋፍ ይውላል ነው የተባለው።
በተጨማሪም አሜሪካ ከግዛቷ ውጭ በተለይም በኢንዶ ፓሲፊክ አካባቢ ‘ለደህንነቴ ስጋት ናቸው’ በምትላቸው አካላት ላይ የምታደርገውን ድንበር ዘለል ቅኝት እና የስለላ ፕሮግራሟን እንድታስቀጥል የሚያስችል ፕሮጀክትን እንደሚደግፍም ዘገባው አመላክቷል።