Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አምባሳደር ምስጋኑ በዶሃ የባላንዳ ምግብ ኢንዱስትሪን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የተመራ ልዑክ በኳታር ዶሃ የሚገኘውን የባላንዳ ምግብ ኢንዱስትሪ የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ ከጉብኝቱ ጎን ለጎን÷ ከኢንዱስትሪው አመራሮች ጋር በግብርና ዘመናዊ አሰራር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን መለዋወጥና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና አቅም ለመጠቀም በኢትዮጵያ እና በባላንዳ ምግብ ኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የባላንዳ የምግብ ኢንዱስትሪ አመራሮችም በኢትዮጵያ ባለው እምቅ አቅም ላይ በቀጣይ ትኩረት እንደሚያደርጉ እና ከሚመለከታቸው የሥራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል።

በውይይቱ ወቅት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እና በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ የሀገሪቱን ግብርና ኢንቨስትመስንት ዕድሎችና የመንግስት ማበረታቻዎች ላይ ተጨማሪ ገለጻ አድርገዋል፡፡

የባላንዳ ምግብ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማራ ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን እንደሚደሰጡም አረጋግጠዋል።

የባላንዳ ምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በኳታር ትልቁ የወተት ውጤቶች እና መጠጦች አምራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version