ጤና

የሕጻናት የምግብ ፍላጎት መቀነስና መፍትሄው

By Amele Demsew

December 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕጻናት ላይ የሚስተዋለው የምግብ ፍላጎት መቀነስ ችግር በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ህጻናትን ለምግብ ፍላጎት መቀነስ ከሚዳርጓቸው ምክንያቶች መካከል ፦ተፈጥሯዊ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚከሰት የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ በንጥረ ነገሮች እጥረት ፣ ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ ምክንያት የሚፈጠር የምግብ ፍላጎት መቀነስ ይጠቀሳሉ፡፡

የተለያዩ ህመሞች ሲባል÷ ጥርስ ማብቀል፣ የቶንሲል፣ የአንጀት፣ የሽንት ቧንቧ፣ የጆሮ ኢንፌክሽን፣ የአንጀት ጥገኛ ትላትሎች፣ የልብ፣ የነርቭ፣ የኩላሊት፣ የጉበት ህመም፣ ደም ማነስ እና የጨጓራ ህመምን ያጠቃልላል ፡፡

የቫይታሚኖች፣ ማግኒዥየም፣ ካልሺየም፣ ዚንክ እና የሌሎች ንጥረ ነገሮች እጥረት ለምግብ ፍላጎት መቀነስ አጋላጭ ምክንያቶች መሆናቸውንም የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ጭማቂ፣ ወተት፣ አጥሚት፣ ጣፋጭ ነገሮች፣ የታሸገ እና ፈሳሽ ምግቦች ከአንድ ዓመት በላይ ለሆናቸው ሕጻናት አብዝቶ መስጠት የሕጻናትን የምግብ ፍላጎት እንደሚቀንስም ይጠቀሳል፡፡

ከሁለት እስከ ስድስት ዓመት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሕጻናት በቀን ከ 120 እስከ 180 ሲ ሲ በላይ ጭማቂ መውሰድ እንደሌለባቸውም ይመክራሉ፡፡

ሌላው የህጻናት የምግብ ፍላጎት መቀነስ መንስኤ ደግሞ በተደጋጋሚ ጣፋጭ ነገሮችን ሲወስዱ ምግብ የመመገብ ፍላጎታቸው እንደሚቀንስ እና ለአላስፈላጊ ውፍረት እንደሚያጋልጥ ይነሳል፡፡

የሕጻናት የአዕምሮ እና የአካል ዕድገት እንዲፋጠን፣ ሰውነታቸው ጠንካራ እንዲሆን እንዲሁም የተመገቡት ምግብ በአግባቡ እንዲፈጭ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉም ይመከራል፡፡

ሌላው ምክንያት ደግሞ በአንድ ዓመታቸው እስከ 7 ኪሎ ግራም በዓመት ሊጨምሩ እንደሚችሉ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን÷ ሁለተኛ ዓመታቸው ላይ ግን የሚጨምሩት 2 ኪሎ ግራም ብቻ በመሆኑ በዚህ ምክንያት የምግብ ፍላጎት መቀነሱ ተፈጥሯዊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የምግብ ፍላጎታቸውን ለመጨመር ለሁሉም ሕጻናት እኩል ላይሠሩ ስለሚችሉ የምግብ ፍላጎት የቀነሰበትን ምክንያት መለየቱ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑንም የኸልዝ ላይን መረጃ ይጠቁማል፡፡

ቅባት የበዛው ምግብ ያለመመገብ፣ ጣፋጭ ነገርን አለማብዛት፣ ትኩረት የሚወስዱ ነገሮችን ማስወገድ ፣ለዓይን የሚስቡ ምግቦችን በማዘጋጀት በትንሽ ትንሹ መመገብና በመሳሰሉት መንገዶች የሕጻናትን የምግብ ፍላጎት ለማስተካከል እንደሚያግዙ የዘርፉ ባለሙዎች ይመክራሉ፡፡