ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ የሀውቲ አማጺያን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች

By Mikias Ayele

December 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከየመን ሀውቲ አማጺያን የተላኩ ናቸው ያለቻቸውን ሁለት ሰውአልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን አስታውቃለች፡፡

የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዳስታወቀው÷ የአሜሪካ ባህር ሀይል ከሀውቲ አማጺያን የተላኩ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ ጥሏል።

የተወሰደው እርምጃ አማጺያኑ በአሜሪካ የንግድ መርከብ ላይ ቀደም ሲል ለፈፀሙት ጥቃት ምላሽ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

በሀውቲ አማጺያን የተላኩ እና የአሜሪካን የንግድ መርከቦች ለመምታት ተልዕኮ የነበራቸው ሁለት ሰው አልባ አወሮፕላኖች የአሜሪካን መርከቦች ሲያስሱ እንደነበር ተነግሯል።

ነገር ግን የአሜሪካ ባህር ሀይል በወሰደው እርምጃ የመርከቦችን ደህንነት ማስጠበቅ መቻሉን ማዕከላዊ ዕዙ አመልክቷል።

ሰሜናዊ የመንን በብዛት የተቆጣጠሩት ሀውቲዎች ወደ እስራኤል ሎጀስቲክ ያደርሳሉ ባሏቸው የአሜሪካ መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡

በዚህም የአሜሪካ መርከቦች በመካከላው ምስራቅ እና በቀይ ባህር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እያደናቀፉ ነው መባሉን አረብ ኒውስ አስነብቧል፡፡