Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት እስከ ድል ድረስ አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ዓለም አቀፍ ጫናዎች ቢኖሩባትም ከሃማስ ጋር የጀመረችውን ጦርነት እስከ መጨረሻው ድል ድረስ አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስታወቁ፡፡

በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ሳቢያ በጋዛ የሚስተዋለው ሰብዓዊ ቀውስ መባባሱን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራትና ተቋማት መሪዎች በእስራኤል ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለአብነትን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን÷ እስራኤል በምትፈጽመው የቦምብ ጥቃት በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ ያላት ድጋፍ እየቀነሰ መምጣቱን አስገንዝበዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔም እስራኤል እና ሃማስ በፍጥነት ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ያቀረበው ሐሳብ በአብላጫ ድምፅ መጽደቁ ተጠቁሟል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ እስራኤል ዓለም አቀፍ ጫና ቢደርስባትም እንኳን ከሃማስ ጋር የጀመረቸውን ጦርነት እስከ ድል ድረስ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

እስራኤል ከተመድ ጋር ያላት ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉም የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ ውድቅ አድርገዋል፡፡

ጦርነቱ አሁንም በጋዛ መቀጠሉን ጠቅሰው÷ በዚህም የእስራኤል ወታደሮች የሃማስ ታጣቂዎችን ድል እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡

የተጀመረው ጦርነት ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ወደ ጎን በመተው ሃማስ እኪጠፋና እስራኤል አስተማማኝ ድል እስክትጎናጸፍ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

በእስራኤል ሃማስ ጦርነት እስካሁን በጋዛ የ18 ሺህ 600 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥም 70 በመቶዎቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በጦርነቱ 50 ሺህ በላይ ዜጎች ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

በአሁኑ ወቅትም በጋዛ ጤና ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ላይ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተመላክቷል፡፡

 

Exit mobile version