ቴክ

ቲክ ቶክ 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

By Mikias Ayele

December 13, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይናው ኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ኩባንያ ቤትዳንስ ይዞታ የሆነው ቲክ ቶክ ከዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎች 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ይህም ከስልክ ጌሞች ውጭ ከዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ የሰበሰበ የመጀመያሪው መተግበሪያ ስለመሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

የመተግበሪያዎች መረጃ አቅራቢ (አፕ ኢንተለጀንስ) እንዳስታወቀው÷ ካንዲ ክራሽ፣ ሆነር ኦፍ ኪንግስ፣ ሞንስተር ስትራይክ እና ክላሽ ኦፍ ክላንስ የተባሉ የሞባይል ጌሞች ከፍተኛ ገቢ በማግኘት በቅደም ተከትል የተቀመጡ የጨዋታ መተግበሪያዎች ናቸው፡፡

በተለይም ካንዲ ክራሽ ጌም ከጎግል ፕሌይ ስቶር እና ከአፕል አይኦኤስ አፕ ስቶር 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተመላክቷል፡፡

በአንፃሩ ቲክ ቶክ ከሞባይል ጌም ውጭ ከዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎቹ  በቀን 11 ሚሊዮን እንዲሁም በዓመቱ መጨረሻ ደግሞ 10 ቢሊዮን ዶላር መሰብሰብ የቻለ ሲሆን ኩባንያው በ2024 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ለመስብሰብ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ኩባንያው በ2024 ተጠቃሚዎች በየወሩ 40 ሰዓታትን በቲክ ቶክ እንዲያሳልፉ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ቲክ ቶክ በሀገረ አሜሪካ እንዳይተገበር ማዕቀብ የተጣለበት ሲሆን ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መንግስት ተደጋጋሚ ክስ ቀርቦበት ማሸነፉን ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡