አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ለታጠቁ ኃይሎች ያቀረበውን የሠላም ጥሪ ለማስተግበር የሚያስችል የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ የሕዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሞላ ሁሴን ÷ መንግሥት የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በውይይትና በንግግር ለመፍታት የሠላም ጥሪ ማቅረቡን አስታውሰዋል፡፡
የታጠቁ ኃይሎች በየጊዜው የሚቀርቡ የሠላም አማራጮችን ወደ ጎን በመተው በክልሉ ሕዝብና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመቀልበስ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የሕግ ማስከበር ሥራ በመሥራቱ አሁን ላይ አንጻራዊ ሠላም መገኘቱንም አመላክተዋል፡፡
የፖለቲካ አመራሩ በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር በንግግርና በውይይት ለመፍታት ባዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሠላም ጥሪ እንዲቀርብ መጠየቁን አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በትናንትናው ዕለት የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄና የራሱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቆም ለሰባት ቀናት የሚቆይ የሠላም ጥሪ አቅርቧል ብለዋል፡፡
የዛሬው ውይይት ዓላማም በቀረበው የሠላም ጥሪ መሠረት በከተማዋ ዙሪያ የሚንቀሰቃሱ የታጠቁ ኃይሎች የሠላም ዕድሉን እንዲጠቀሙ ማስቻል መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!