Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ወደ 11 ቢሊየን ብር አደገ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር ማደግ መቻሉን ባንኩ ገልጿል።

ባንኩ በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ 15 ትራክተርና 10 ኮምባይን ሀርቨስተር እንዲሁም በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ደንበኞቹ 14 ኤክስካቫተር በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አቅርቧል።

የኮምባይን ሀርቨስት መሳሪያዎቹ 72 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ሲሆን÷ትራክተሮቹ ከ43 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ኤክስካቫተሮቹ ከ87 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ መሆናቸውንም ባንኩ አስታውቋል።

በርክክቡ ወቅት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)÷ ባንኩ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ አገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች ወደ ሥራ ለተሰማሩ ዜጎች የሚያደርገው ድጋፍ እድገት እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከያዘው 51 ቢሊየን ብር ውስጥ 15 ቢሊየን ብር ለግብርና ዘርፉ የተመደበ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የተደረገው የመሳሪያ ርክክብ የግብርና ሜካናይዜሽንን በማጠናከር የምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ጠቅሰዋል፡፡

በማዕድን ዘርፉ የተሰጡ መሳሪያዎችም አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ሰፊ ዕድል እንድትጠቀም የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው÷በሊዝ ፋይናንሲንግ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ባንኩ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከነበረበት 2 ቢሊየን ብር ወደ 11 ቢሊየን ብር ማደጉንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version