አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በወጡ የአፈፃፀም መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በተገኘበት እና የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን የነበሩ ጥንቃቄዎች አሁን ላይ መዘናጋት እየታየ መሆኑን አስታውቋል።
መንግስት በሽታዉን ለመከላከልና ስርጭቱን ለመቀነስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዉጆ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል።
ሆኖም አብዛኛው ህብረተሰቡ የመዘናጋት፣ የቸልተኝነትና በሽታዉን አስመልክቶ የሚሰጡ ትእዛዛቶች ወደ ጎን በመተዉ የሚሰጡ መግለጫዎችን የመላመድና ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎች እየተስተዋለ ይገኛል ብሏል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፡፡
በዚሁ መሰረትም በመመሪያ በኮድ 2 የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ከፊል የእንቅስቃሴ ክልከላ ፣የማሰክ አጠቃቀም ፣ በአገር አቋራጭ የህዝብ ተሸከርካሪዎች ላይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች መግቢያና መውጫ ስአት ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ግለሰቦች ቤታቸዉ እንዲዉሉ በማድረግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ታሳቢ ተድርጎ የቤት ተሸከርካሪዎች ላይ በሙሉና በጎዶሎ መለያ ቁጥር ከፊል እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
ሆኖም የኮድ 2 ተሸከርካሪ ባለቤቶች በታሰበዉ መልኩ ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ የህዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም እና ታርጋዎችን እየቀያየሩ የመጠቀም ሁኔታ መታየቱ እንዲሁም ተራቸዉ ባልሆነ ቀን ቤታቸዉ ከመዋል ይልቅ በሰፊዉ የመንቀሳቀስ ሁኔታ ተስተውሏል ብሏል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ።
በመሆኑም በአጠቃላይ በኮድ ሁለት የቤት ተሸከርካሪዎች ተጥሎ የነበረዉ ክልከላ ተነሰቶ አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴውን ለመገደብ የሚያስችል አማራጭ ክልከላ እንድተገበር የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወስኗል፡፡
በተመሳሳይ የእንቅስቃሴ ገደብ መቀነሻ አሰራሮች አንዱ በሆነዉ በሀገር አቋራጭ ተሸከሪካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ላይም መሻሻያ ተደርጓል፡፡
የዋጋ ጭማሪ ማድረግም ሰዎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ለመገደብ አሰተዋጽኦ እንደሚያደረግ በትራንስፖርት ሚኒስቴር የተደረገው ጥናት ያመላክታል፡፡
በዚሁ መሰረት አገር አቋራጭ መደበኛ የወንበር አቅማቸዉ ከ45 ሰዉ በላይ የሆኑ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ከመደበኛ ዋጋዉ 75 በመቶ እንዲሆን የተወሰነ ሲሆን መደበኛ የወንበር ቁጥራቸዉ እስከ 45 ሰው የሆኑ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች የሚያስከፍሉት የታሪፍ ጭማሪ ደግሞ በ100 ሆኖ ተወሰኗል፡፡
ከዚህ ባለፈ የሚኒስትሮች ኮሚቴ በተሻሻለዉ መመሪያ መሰረት የማስክ አጠቃቀምን አስመልክቶ ከቤት ዉጭ በማንኛዉም ቦታ የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግን ግዴታ እንዲሆን ወስኗል፡፡
የአፍና አፈንጫ መሸፈኛ ማሰክ በፋብሪካዎች የተሰራ ወይም ባህላዊ ጨርቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህን ግዴታ በማሰፈጸም ረገድ የጸጥታ መዋቅሩ ኃላፊነት እንዳለበት ተወሰኗል፡፡
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያ ስአት 1 ሰዓት ከ30 እንዲሆን የተቀመጠ ሲሆን መውጫ ስአቱም 9 ሰዓት 30 እንዲሆን ተደርጎ ተሸጋሽጓል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነትና ግዴታ
እንዳለበት ያሳሰበው ዐቃቤ ህግ የሚታዩ መዘናጋቶችን እና ችላ ባይነትን መቅረፍ እንደሚገባ አሳስቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።