Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያን ወደ ፈጠራና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ለመምራት እየተሰራ ነው – በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያን ወደ ፈጠራ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ለመምራት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ዶ/ር ገለጹ፡፡

በማይክሮሶፍት ካምፓኒና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ዲጂታል ልማት ፕሮግራም ለመደገፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የውይይት ፎረም ተካሂዷል፡፡

የውይይቱ አላማ የኢትዮጵያን ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በተመለከተ በአቅም ግንባታ፣በልምድ መጋራት እንዲሁም ስልታዊ የትግበራ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት የትብብር ስራ ለመስራት ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን የመሪነት ሚና እንድትጫወትና ወደ ፈጠራና ዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግር ለመምራት እየተሰራ ነው።

በተጨማሪም÷ተቋማቸው ለኢትዮጵያ ብሩህ፣ አካታች እና የበለጸገ ዲጂታልን ለማረጋገጥ ከማይክሮሶፍት የዲጂታል ልማት ፕሮግራም ማዕቀፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በትብብር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

አሌክሳንደር ጆሴ ፒንሆ የማይክሮሶፍት ካምፓኒ በተባበሩት መንግስታት የአለማቀፍ ኃላፊ በበኩላቸው÷ ማይክሮሶፍት የዲጂታል ልማት ፕሮግራም ቴክኒካል ክህሎት፣ ዲጂታል አገልግሎቶች እና የአቅም ግንባታ ስልጠና መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

ይህም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገራት ለመደገፍ ወሳኝ ሚና እንዳለው በመጠቆም በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር በትኩረት እንደሚሰሩ አጽኖት ሰጥተዋል፡፡

የማይክሮሶፍት ዲጂታል ዴቨሎፕመንት ፕሮግራም ፎረም እና ወርክሾፕ በነገው እለትም እንደሚቀጥል ጠገልጿል፡፡

በቀጣይ ውይይት እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አብሮ የሚሰሩ ጉዳዮች ላይ እንደሚመክር ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version