ዓለምአቀፋዊ ዜና

አፍሪካ በአንድ የመገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም ልትመክር ነው

By Alemayehu Geremew

December 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሀገራት በአንድ የመገበያያ ገንዘብ መጠቀም በሚያስችላቸው ሥርዓት ላይ ሊመክሩ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የሀገራቱ ምክክር የአፍሪካን የገንዘብ ኅብረት በፍጥነት ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችል የአፍሪካ ኅብረት መረጃ አመላክቷል፡፡

የሥርዓቱ ዕውን መሆን የአፍሪካን ማዕከላዊ ባንክ ፣ የአፍሪካን ኢንቨስትመንት ባንክ እና የአፍሪካን የገንዘብ ፈንድ ለማቋቋም ያስችላል ተብሏል፡፡

በምክክሩ የአፍሪካ የገንዘብ ሚኒስትሮች፣ ማዕከላዊ ባንኮች፣ የተለያዩ የአፍሪካ ኅብረት ቅርንጫፍ አካላት እና ኤጀንሲዎች ፣ ቀጣናዊ የምጣኔ ሐብት ማኅበራት፣ የአፍሪካ የማዕከላዊ ባንኮች ማኅበር፣ የአፍሪካ የደኅንነት ዋሥትና ማኅበራት እና የልማት አጋሮች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የመገበያያ ኅብረቱ ዕውን መሆን የሀገራቱ የመገበያያ ምንዛሬ የተረጋጋ እንዲሆን ለመቆጣጠር ፣ የውጭ ምንዛሬ ገደቦችን ለማስወገድ እና በምጣኔ ሐብት ለመዋሃድ ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡

ጉባዔው በነገው ዕለት በዛምቢያ ሉሳካ ይጀመርና አርብ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡