የሀገር ውስጥ ዜና

የአሳይታ- አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 94 በመቶ ተጠናቀቀ

By Amele Demsew

December 12, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሳይታ-አፋምቦ-ጅቡቲ ድንበር መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 94 በመቶ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ የአፈር ጠረጋ እና ቆረጣን ጨምሮ የሰብ ቤዝ ስራ ፣ የቤዝኮርስ ፣ የውሃ ማፋሰሻ ፣ የስትራክቸር ፣ የመንገድ ዳር ምልክቶች መትከል እና ቀለም መቀባት ስራዎች ከሞላ ጎደል የተከናወኑ ሲሆን ÷ የ46 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ማንጠፍ ስራም ተካሂዷል፡፡

የፕሮጀክቱ አካል የሆኑት የሦስት ድልድዮች ግንባታም ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል።

የመንገዱን ግንባታ ለማከናወን የተመደበው በጀት 1 ቢሊየን 600 ሚሊየን 901 ሺህ 379 ነጥብ 89 ብር ወጪ ሙሉ ለሙሉ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የመንገዱ ርዝማኔ 50 ነጥብ 34 ኪሎ ሜትር ፤ የጎን ስፋቱ ትከሻን ጨምሮ በገጠራማ ሥፍራዎች 10 ሜትር ፣ በወረዳ ከተሞች 19 ሜትር እና በዞን 21 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት እንዳለው የተገለጸ ሲሆን÷ ግንባታው በሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ እየተከናወነ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

መንገዱ በዋናነት ኢትዮጵያን በአሳይታ በኩል ከጅቡቲ ጋራ በቅርበት የሚያስተሳስር እንዲሁም አሳይታ ከተማን ከአፋምቦ ወረዳ ብሎም በርካታ ቀበሌዎችን በማገናኘት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ይበልጥ ያጠናክራል ተብሏል።

አዲሱ የመንገድ ፕሮጀክት አሁን ላይ ያለውን የሚሌ – ዲቼ ኦቶ – ጋላፊ – ጅቡቲ ወደብ መንገድ በ 30 ኪሎ ሜትር የሚያሳጥር ሲሆን÷ ወደ ጅቡቲ ለመሄድ እንደ ተጨማሪ አማራጭ መንገድም ሆኖ እንደሚያገለግል አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

#Ethiopia ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!