ዓለምአቀፋዊ ዜና

ተመድ በ2024 ለሰብዓዊነት የሚውል 46 ቢሊየን ዶላር ያሥፈልገኛል አለ

By Alemayehu Geremew

December 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአዲሱ የፈረንጆቹ ዓመት ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል 46 ቢሊየን ዶላር ያሥፈልገኛል ብሏል፡፡

በዛሬው ዕለት የተባለውን ገንዘብ የጠየቀው በዓለምአቀፍ ደረጃ የተንሰራፋውን ግጭት እና መፈናቀል ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ድርጅቱ በፈረንጆቹ 2024ትም በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ፍልሥጤማውያን፣ ሱዳናውያን እና ዩክሬናውያን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸውም ከወዲሁ ከግምት ውስጥ አስገብቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንዳስታወቀው ፥ በ2024 በግጭቶች፣ ከዓየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በሚከሰት የተፈጥሮ አደጋ እና በድሕነት ሰበብ ወደ 300 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋሉ።

74 ነጥብ 1 ሚሊየን የሚሆነው ሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ በምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የሚኖረው ሕዝብ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ከተጠቀሰው አኀዝ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዘው በሱዳን ግጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሕዝብ መሆኑም ተገልጿል፡፡