አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳዑዲ አረቢያ በተያዘው ወር የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ ብቻ በሃውቲ አማጽያን የተቀበሩ 733 ፈንጂዎችን አምክኛለሁ ብላለች፡፡
ማሳም የተባለው የሳዑዲ ፈንጂ አምካኝ ፕሮጀክት እንዳስታወቀው÷ ፕሮጀክቱ በፈፀመው ተልዕኮ 618 ቀደም ሲል ተጠምደው ያልፈነዱ618፣ ፀረ ታንክ ፈንጂዎች 110 እንዲሁም 4 ፀረ ሰው ፈንጂዎችና አንድ ተቀጣጣይ ፈንጂ መክኗል።
በሃውቲ አማጽያን የተጠመዱት እነዚህ ፈንጂዎች በየመን የሚገኙ ህጻናትን፣ ሴቶችና አዛውንቶችን ጨምሮ በንፁሃን ዜጎች ህይወት ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥረው መቆየታቸው ተመላክቷል።
የማሳም ፈንጂ አምካኝ ፕሮጀክት በሳዑዲ አረቢያው ንጉስ ሞሃመድ ቢን ሳልማህ ትዕዛዝ የሚተገበረው በየመን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ እና መንገዶችን የማስከፈት የተያዘው ፕሮጀክት አካል መሆኑም ተገልጿል፡፡
የፈንጂ ማመክን አፕሬሽኑ አማጽያኑ ይገኙባቸዋል በተባሉት ማሪብ፣ በአደን፣ ጁፍ፣ ሻብዋ፣ ታይዝ፣ ሆደይዳህ፣ ላሂጅ፣ ሰነዓ፣ አል-በይዳ፣ አል-ዳሌ እና ሰአዳ በተባሉ አካባቢዎች መካሄዱም ነው የተገለፀው፡፡
ፕሮጀክቱ ስራ ከጀመረበት 2018 ጀምሮ እስካሁን 424 ሺህ 147 ፈንጂዎችን ማምከን መቻሉን የተገለፀ ሲሆን ሳዑዲ 33 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ ፕሮጀክቱን ለአንድ አመት ለመቀጠል ቀደም ሲለ መወሰኗን አረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡