Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አቶ ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዡ ቢንግ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ለጀመረችው ሁለንተናዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዕውን መሆን ቁርጠኛ መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ለምታደርገው ቀጣይነት ያለው የልማት አጋርነትም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በአፍሪካ የጸጥታ፣ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እያደረገች ላለው ገንቢ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም ቻይና በባለብዙ ወገን መድረኮች የምታደርገውን በመርህ ላይ ያተኮረ ድጋፍና ኢትዮጵያ ብሪክስን እንድትቀላቀል ላደረገችው ድጋፍም እውቅና ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ቁርጠኛ መሆኑንም አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ዡ ቢንግ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ሁለንተናዊ፣ ስልታዊና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት ማድነቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደሩ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ሰላምና ልማት ለማስጠበቅ ያላትን ገንቢ ሚና አድንቀው በሀገሪቱ የተጀመረው የሰላም ሂደት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሁለተኛውን የቻይና – የአፍሪካ ቀንድ የሰላም፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ኮንፈረንስ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑንም አምባሳደሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።

Exit mobile version