ቴክ

የአቪዬሽን ኢኖሼሽን ኤክስፖ ተከፈተ

By Shambel Mihret

December 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው የአቪዬሽን ኢኖሼሽን ኤክስፖ ተከፈተ፡፡

ኤክስፖው በዛሬው ዕለት “ፈጠራ፣ ለአቪዬሽን ልህቀት ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተው፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኤክስፖውን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፤ ኢትዮጵያን በአቪዬሽኑ ዘርፍ ተወዳዳሪና የአፍሪካ ማዕከል ለማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተከወኑ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፥ የአቪዬሽን ዘርፉን ቴክኖሎጂ መጠቀም ፣ ሽግግር ማድረግና በራስ አቅም ማጎልበት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል።

ይህንንም ከግብ ለማድረስ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ብሔራዊ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ይህም እንደሀገር በዘርፉ የተወጠነውን ከዳር ለማድረስ በጎ ሚና አለው ነው ያሉት።

የፈጠራ አቅምን የሚያሳዩና እንደሀገር በአቪዬሽኑ ዘርፍ እየተካሄደ ለሚገኘው ሰፊ ስራ በጎ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ የፈጠራ ባለቤቶች ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው ኤክስፖ ይሳተፋሉም ተብሏል።

95 ወጣቶች በተናጥልና በጋራ በሰሯቸው ስራዎች፣ 34 የግልና መንግስታዊ ተቋማት ከሚሳተፉት መካከል ናቸው።

ከኤክስፖው ጎን ለጎን የፓናል ውይይትና በፈጠራ ባለቤቶች መካከል ውድድር ይካሄዳል የተባለ ሲሆን አሸናፊ ለሚሆኑ 15 የፈጠራ ባለቤቶች ዘላቂ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል።

በኤክስፖው ላይ የአቪዬሽን ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የፈጠራ ውጤቶች፣ ምርቶችና አገልግሎቶች ቀርበዋል፡፡

በመራኦል ከድር