የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ የአመራር ልኅቀት አካዳሚ ለዲፕሎማቶች ማብራሪያ እየሠጠ ነው

By Alemayehu Geremew

December 11, 2023

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ የአመራር ልኅቀት አካዳሚ ዓላማና ተግባርን የተመለከተ ማብራሪያ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እየተሰጠ ነው።

ገለጻውን ያደረጉት የአካዳሚው ርዕሰ አካዳሚ ዛዲግ አብርሃ ናቸው፡፡

አካዳሚውን በተመለከተ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

የአካዳሚው ቀጣይ ራዕይ ትልቅ መሆኑን ለዲፕሎማቶች ያብራሩት ርዕሰ አካዳሚው በቀጣይም አካዳሚውን ለማጠናከር እና ከሌሎች መሠል ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አንስተዋል።

በተለይም አካዳሚው ከጥናትና ምርምር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

አካዳሚው እስከ አሁን 48 የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄዱን በመጥቀስም፥ ባለፉት ሁለት ዓመታት 9 ሺህ 522 ከፍተኛ አመራሮችን ማሠልጠን መቻሉንም አስረድተዋል።

ከዚህ ባለፈም የሴቶችን የአመራር አቅም ማሳደግን ያለመ ስኬት ተከናውኗል ነው ያሉት።

በዚህ የዓመራር ልኅቀትን በማሳደግ ሂደት ውስጥ ከሀገራት እና ተቋማት ጋር የጋራ ትብብሮች መኖራቸውንም አቶ ዛዲግ አንስተዋል።

በይስማው አደራው