Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ጋር በዋሺንግተን ሊወያዩ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ በነጩ ቤተ መንግስት ለሶስተኛ ጊዜ በነገው እለት ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑን ኋይት ሃውስ አስታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር ተገናኝተው በዩክሬን ሊደረግ በሚገባው እርዳታ ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፕሬዚዳንት ዜለንስኪ ጉብኝት የአሜሪካ ኮንግረስ ለዩክሬን አስቸኳይ እርዳታ ይፋ ለማድረግ እየተወያየ ባለበት ወቅት የተደረገ መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡

ፕሬዚዳንቱ በነገው እለት ሁሉም ሴናተሮች በተገኙበት ንግግር ያደርጋሉ የተባለ ሲሆን፥ ከሴኔቱ መሪ ቹክ ሹመር፣ ከሪፐብሊካን መሪ ሚች ማክኔል እና ከሴኔቱ ረዳት አመራር እንዲሁም ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ማይክ ጆንሰን ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ ተብሏል፡፡

የኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሪን ዣን ፒየር በሰጡት መግለጫ÷ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዩክሬናውያን ከሩሲያ ራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት አሜሪካ ድጋፍ ለማድረግ ሁልጊዜም ቁርጠኛ መሆኗን ለማሳየት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪው፥ ከዚህ ጋር ተያይዞም የዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ ፍላጎትን በተመለከተ ሁለቱ መሪዎች እንደሚመክሩ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሁለቱ መሪዎች በሚኖራቸው ውይይት ሊኖር በሚገባው የመከላከያ ትብብር ዙሪያ ይመክራሉ መባሉን ሲ ኤን ኤን ዘግቧል፡፡

Exit mobile version