አዲስ አበባ፣ ታኅሣስ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ጤና ድርጅት ሰብዓዊ ዕርዳታ በፍጥነት ወደ ጋዛ እንዲገባ ጥሪ አቀረበ፡፡
ድርጅቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈውን እጅግ አሥፈላጊ የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ጋዛ እንዲደርስ እና ለወራት የዘለቀው ጦርነት እንዲያበቃ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሐሳብ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡
ተመድ ያሳለፈው ውሳኔ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ያልተቋረጠ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በአስቸኳይ ወደ ጋዛ እንዲደርስ የሚጠይቅ ነው፡፡
ዕሁድ የተካሄደው የዓለም ጤና ድርጅት የሥራ አሥፈፃሚ ቦርድ ልዩ ሥብሰባ በቀረቡት ሐሳቦች ላይ ተወያይቶ ሥምምነት ላይ በመድረስ መጠናቀቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በእስራኤል – ሃማስ ጦርነት እስካሁን ወደ 18 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን ለህልፈት መዳረጋቸውን የሆስፒታል ምንጮችን ዋቢ ያደረገው ዘገባ አመላክቷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ በጦርነቱ 80 በመቶ የሚሆኑ የጋዛ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን እና ለምግብ፣ መጠጥ ውሃ እና ለመድሃኒት አቅርቦት ችግር መጋለጣቸውን አስታውቋል።