የሀገር ውስጥ ዜና

ሠራዊቱ ድንበር ከመጠበቅ ባሻገር ህብረተሰቡን ከጎርፍ አደጋ የመታደግ ስራ እየሰራ መሆኑ ተመላከተ

By Amele Demsew

December 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ኢትዮጵያ ድንበር ጥበቃ ተሰማርቶ የሚገኘው ሠራዊት የሀገርን ድንበር ከመጠበቁ ባሻገር የአካባቢውን ህብረተሰብ ከጎርፍ አደጋ የመጠበቅ ስራ እየሰራ መሆኑን የኮሩ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ተሾመ ይመር ገለጹ፡፡

በቀጣናው በደረሰ ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የጎርፍ አደጋ በማጋጠሙ ሠራዊቱ አቅመ ደካሞችን አደጋ ከተከሰተበት አካባቢ በማሸሽ ከሚበላው ሬሽን አካፍሎ በመስጠት ህዝበዊነቱን ማስመስከሩን የኮሩ አዛዥ ተናግረዋል፡፡

አደጋውም በሰው ህይዎትና በንብረት ላይ ጉዳት ያስከተለ ቢሆንም ተጨማሪ ጉዳት ሳያስከትል ሠራዊቱ ፈጥኖ በመድረስ ህብረተሰቡን ከተጨማሪ ጉዳት መታደጉንም ነው የገለጹት ፡፡

ለዚህም የኢፌዴሪ አየር ሃይል የምስራቅ ሪጅን አየር ምድብ ምግብና አልባሳት እንዲሁም ጊዜያዊ መጠለያ በማመላለስ የነፍስ አድን ተግባር መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይም ዝናቡ ያቆመ ቢሆንም በቀጠናው የተገኘው የኢፌዴሪ ባህር ሃይል የተፈናቀሉ ዜጎችን በጀልባ በማጓጓዝ ወደ መኖሪያ ቀያቸው የመመለስ ስራ መሰራቱንም ነው ያነሱት ብርጋዲየር ጄኔራል ተሾመ፡፡

ዝናቡ ባስከተለው ጎርፍ ጉዳት የደረሰበትን ቀላፎ ወረዳ ሠራዊቱ የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስ፣ ከተማውን በማጽዳት መከላከያ ኃይልን ያስመሰገነ ሥራ መሰራቱም ከመከላከያ ሠራዊት የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡