ቴክ

ቴስላ ሳይበር ትራክ የኤሌክትሪክ መኪና

By Alemayehu Geremew

December 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኤሎን መስክ ኩባንያ ከሆኑት አንዱ ‘ቴስላ አውቶሞቲቭ’ ቴስላ ሳይበር ትራክ የተሠኘ በቅርፅም ሆነ በዓይነት የተለየ የኤሌክትሪክ መኪና ለሽያጭ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡

መኪናውን ከሌሎች የኤሌክትሪክ መኪናዎች ለየት የሚያደርገው ጥይት በማይበሳው፣ ቀለም በማያስፈልገው፣ በማይዝግ ስቴይንለስ ስቲል ብረት ስለተሠራ መሆኑን ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የመኪናው መስኮቶች ከተዘጉ ምንም ዓይነት ድምፅ ከውጪ የማያስገቡና ግጭት ቢደርስባቸው በቀላሉ የማይሰበሩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

የመኪናው ጣራ ድርብ ሲሆን በሰፊው ጠንካራ መሥታወት ሰማይን መመልከት ያስችላል፡፡

3 ሺህ 104 ኪሎ ግራም የሚመዝነውና አራት ባለ 20 ኢንች ዙሪያ መጠን ያላቸው ጎማዎች የተገጠሙለት ተሽከርካሪ ነው።

እስከ 1 ሺህ 134 ኪሎ ግራም ክብደት የመጫን እና እስከ 4 ሺህ 990 ኪሎ ግራም የመጎተት ዓቅም አለውም ተብሏል፡፡

መኪናውን በማየት ብቻ ጠንካራ መሆኑን መመስከር እንደሚቻል የተገለጸ ሲሆን፤ የግንባታ ዕቃዎችን መጫን ሲፈልጉ ውስጥ ሆነው በሚሠጡት ዲጂታል ትዕዛዝ ብቻ መኪናውን ወደ “ፒክ አፕ ሞድ” መቀየር ይቻላል፡፡

ወለሉ እጅግ በጣም ጠንካራ በሆነ ንጣፍ የተሠራ በመሆኑ ተጨማሪ ንጣፍ ማሠራት አያስፈልግም ብሏል ኩባንያው፡፡

አራቱም ጎማዎች በራሳቸው ኃይል እንዲሽከረከሩ እና ወደታዘዙበት አቅጣጫ እንዲተጣጠፉ ተደርጎ የተሰራው ይህ መኪና፤ ውስጡ ከፊት ከሾፌሩ ጋር የ2 ሰዎች፣ ከኋላ የ3 ሰዎች መቀመጫዎች አሉት፡፡

መካከል ላይ መኪናው ከፍ ስለሚል ውጭውን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ወለል አድርጎ የሚያሳይ 18 ነጥብ 5 ኢንች ስፋት ያለው ስክሪን ተገጥሞለታል፡፡

9 ነጥብ 4 ኢንች ስክሪን ከኋላ የተካተተለት ይህ መኪና አንድ ጊዜ ቻርጅ ተደርጎ እስከ 550 ኪሎ ሜትር መጓዝ ይችላል ተብሏል።

ባትሪውን በተመለከተ ግን ኩባንያው ዝርዝር መረጃዎችን አላወጣም።

ቴስላ ሳይበር ትራክ የኤሌክትሪክ መኪና እስከ ፈረንጆቹ 2025 የሚቆይ 80 ሺህ ዶላር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡