አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አማካኝነት በኢትዮጵያ የተሰራው የመጀመሪያው ላፕቶፕ ኮምፒውተር የደህንነት ችግሮችን የሚቀርፍ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
አስተዳደሩ የላፕቶፕ፣ ሰርቨር እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሰርቶ ለተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡
የሳይበር ደሕንነትን ለማስጠበቅ የቴክኖሎጂ ባለቤት መሆን ምርጫ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ ነው በዘርፉ ባለሙያዎች የሚነሳው፡፡
በዚህም የሳይበር ደህንነትን ከማስጠበቅ በተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅምን ከፍ ለማድረግ እና ተጽዕኖ ለመፍጠር ያስችላል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ሲስተም ሴኪዩሪቲ ባለሙያ ደመቀ ገ/ኢየሱስ እንዳሉት ፥ አብዛኛውን ጊዜ ኮምፒውተሮች ሲሰሩ እንደየሀገራቱ የተለየ ዓላማ ይኖራቸዋል፤ ጥቃት ይሰነዘርባቸዋል ፤ ክፍተቶችም ይታዩባቸዋል፡፡
አስተዳደሩ ሌላ ሀገር የተሰራ ላፕቶፕ ኮምፒውተር መጠቀሙ አደጋ እንዳለው ባለሙያው ጠቅሰው፥ ይህን ችግር ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የራስን ቴክኖሎጂ መያዝ ያስፈልጋልም ነው ያሉት፡፡
በዚህም ላፕቶፕ ኮምፒውተሩ የደህንነት ችግሮችን ለመቅረፍ በራስ ኢንጂነሮች የተሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።
ኮምፒውተርም ለአያያዝ ምቹ፣ ቀላል፣ የሚለጠፍ፣ የራሱን ሎጎ የያዘ፣ ክፍተቱ ወይም ጥቃት እንዳይደርስ ራሱን በየጊዜው እንደሚያዘምንም ነው የተገለጸው፡፡
ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች የሰራችው ላፕቶፕ የይቻላል መንፈስን ለአሁኑ ትውልድ ትምህርት የሚሆን ሲሆን ፥ ለቀጣይ ትውልድ ደግሞ ይህን መነሻ በማድረግ የራሱን ማዘመኛ ተጠቅሞ ሀገርን የሚያስጠራበት እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
ገበያ ላይ ካሉት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችም በአስተዳደሩ የተሰራው ላፕቶፕ አጠቃቀሙን ሀገርኛ በማድረግና የተለያዩ መለያዎች አሉት ተብሏል፡፡
ሆኖም እነዚህ ኮምፒውተሮች እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደገበያ የማውጣት እቅድ እንደሌለ ያነሱት ባለሙያው ፥ ተቋሙ ዋና ዓላማው አድርጎ የያዘው ደህንነትን ማስጠበቅ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን አመርታለሁ የሚል ተቋም ቢመጣ አስተዳደሩ የማረጋገጥ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም አሁን ከተሰራው በተሸለ መልኩ ብዙ መለያዎች ያሉት፣ ቀልጣፋ፣ የዘመነ ላፕቶፕ ኮምፒውተር እየመጣ ነው ማለታቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡