Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ከዓለም ባንክ ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢጀርድና ከዓለም ባንክ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ÷ በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚና የልማት ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በወቅቱ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ባላት የህዝብ ብዛትና የተፈጥሮ ሀብት በምስራቅ አፍሪካ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት በመሆኑ የልማት አጋሮች በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በክፍለ አህጉር ደረጃ እንዳደረጉት ኢንቨስትመንት ይቆጠራል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ያላት የልማት ትብብር ውጤታማ መሆኑንና እስካሁን በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርምን ውጤታማነት ለማረጋገጥ፣ የግል ዘርፉን ለማጎልበት፣ የመልሶ ማቋቋምን ተግባራዊ ለማድረግ የአለም ባንክ ድጋፍ እንዲያደርግ አቶ አህመድ ሽዴ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ÷ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለማጠናከር፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የኢኮኖሚ ትስስር ለማጎልበትና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን ለማፋጠን ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡

የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢጀርድ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማድረግ፣ የግል ዘርፉን ለማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ለማስፋፋት፣ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ለማጠናከርና የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት የአለም ባንክ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል፡፡

Exit mobile version