አዲስ አበባ፣ ሕዳር 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ወደ ትግበራ መግባቱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ ገለጸ።
በቢሮው የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ቡድን መሪ አቶ ሚካኤል ሐጎስ÷ በተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም የሚተገበሩ 16 የጤና ኤክስቴንሽን ማዕቀፎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ይረዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ፕሮግራሙ ወደ ሥራ የገባው ከ45 ሺህ በላይ የጤና ልማት ቡድን አባላትን በአዲስ መልክ በማደራጀትና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ነው ብለዋል።
ከ100 በላይ የሚሆኑ የቤተሰብ ጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችም የሙያ ብቃት ማሻሻያ ሥልጠና ተከታትለው ቡድኖቹን ለመምራትና ለማስተባበር ወደ ትግበራ መግባታቸውንም ገልጸዋል።
እንዲሁም 500 የሚሆኑ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሁለት ወራት ሥልጠና እየተከታተሉ መሆናቸውን የቡድን መሪው አመልክተዋል።
ለክልሉ ጤና ኬላዎች 150 ኪት የሕክምና መሣሪያዎች መከፋፈሉንም ጠቁመዋል።
በክልሉ ቀደም ብሎ በተከሰተው ችግር አገልግሎት አቋርጠው የቆዩ 58 ጤና ኬላዎችን መልሶ ለመገንባት እንቅስቃሴ እንደተጀመረም ቡድን መሪው አስታውቀዋል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!