Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢራን ለጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒ ግድያ 50 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈል ጠየቀች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዓመታት በፊት በኢራኑ ጄኔራል ቃሲም ሱለይማኒ ላይ በተፈጸመው ግድያ እጃቸው አለበት በሚል ኢራን የጠረጠረቻቸው አሜሪካና ሌሎች ግለሰቦች 50 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ የኢራን ፍርድ ቤት ጠይቋል፡፡

የኢራን ውድ ልጅ እና የጸረ-ሽብር አዛዥ የነበሩት ሌተናንት ጄኔራል ቃሴም ሱሌይማኒ ከሦስት ዓመታት በፊት በባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ በሰው አልባ አውሮፕላን ተመትተው ህይዎታቸው ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡

የቴህራን ፍትህ ዲፓርትመንት ከጄኔራሉ ግድያ ጋር በተያያዘ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት እና በርካታ ግለሰቦችን ጨምሮ በአጠቃላይ በ42 ተከሳሾች ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡

ከተከሰሾቹ መካከል የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ፣ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ማርክ ኢስፔር፣ በኢራን የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ ተወካይ ብራያን ሁክ ይገኙበታል ተብሏል፡

በተጨማሪም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ ደኅንነት ኤጀንሲ (NSA)፣ የማዕከላዊ መረጃ ኤጀንሲ (ሲአይኤ)፣ የፌደራል ሪዘርቭ ሲስተም ሃላፊዎች በጄኔራሉ ግድያ የተከሰሱ ተቋማት ናቸው፡፡

በዚህም ተከሰሾቹ 50 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ የተወሰነ ሲሆን 16 ቢሊዮን ዶላሩ በጄኔራሉ ግድያ ለደረሰው የገንዘብ እና የሞራል ካሳ እንዲሁም 34 ቢሊዮኑ ደግሞ ተከሳሾቹ ለወደፊት ለሚፈፅሟቸው የህግ ጥሰቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚውል ነው ተብሏል፡፡

ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ ተከሳሾቹ  መላው ኢራናውያን ዜጎችን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ውሳኔው ተከሳሾቹ በሌሉበት የተላለፈ ሲሆን ውሳኔውን በመቃወም በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚቻል ፍርድ ቤቱ ማስታወቁን ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version