የሀገር ውስጥ ዜና

ከለውጡ ወዲህ እየተተገበረ ያለው ፌዴራሊዝም የሕዝቦችን ፍላጎት መመለሱ ተመላከተ

By Alemayehu Geremew

December 07, 2023

ከለውጡ ወዲህ እየተተገበረ ያለው ፌዴራሊዝም የሕዝቦችን ፍላጎት መመለሱ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በለውጡ ማግስት ኢትዮጵያ ውጤታማ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ተግባራዊ በማድረጓ ብዝኀነትን እና የሕዝቦችን መልከ-ብዙ ፍላጎቶች መመለስ ችላለች ተባለ።

ኢትዮጵያ የብዝኀነት ሀገር በመሆኗ ነገን ከግምት ያስገባ፣ ዛሬ ላይ ያሉ መልከ-ብዙ ፍላጎቶችን ማስተናገድ የሚችል ከሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት የመነጨ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተግባራዊ እያደረገች መሆኗንም ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ እና የሕግ ምሁር ማሩ አብዲ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት÷ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ከሕገ-መንግሥት የተሰፈረ የሥልጣን ተዋረድ እና ውክልና ያለው መንግሥት እንዲሁም የተከፋፈለ ፍላጎት ያላቸው ሕዝቦች በጋራ የሚኖሩበትን መንገድ የሚያመቻች ሥርዓት ነው።

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት የውክልና እና የማንነት ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሐሳብ እና የታሪክ እውነታዎችን እንዲሁም የፍላጎት ብዝኀነትን ጭምር እያስተናገደ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም ብሔረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና ማግኘታቸው፣ የሐሳብ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት አግባብ እንዲሁም ተዳፍነው የቆዩ የክልልነት ጥያቄዎች በተግባር የተፈቱበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በመራኦል ከድር