አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊ፣ ምክንያታዊና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሐመድ አል አሩሲ አስገነዘቡ፡፡
ጥያቄውና ፍላጎቱ ሠጥቶ መቀበልን ጨምሮ ሠላማዊ ማዕቀፍና አካሄድን የተከተለ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው በቀጥታ የዜጎችን ሕይወት የሚነካ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የማንንም ጎረቤት ሀገር ሉዓላዊነት የማይነካና ሠላማዊ አማራጭን የተከተለ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄ ፍትሐዊነትን መሠረት ያደረገና የመጨረሻ ግቡም በጋራ መልማትና መጠቀም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጎረቤት ሀገራትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት ከሁሉም አቅጣጫዎች በቅን ልቦና ሊያዩት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡