አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አራት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የባለስለጣኑ ዋና ዳይሬክተር መለሰ ኪዊ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ በአራት ወራት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
የዕቅዱን 85 በመቶ ማሳካት መቻሉንም አመላክተዋል፡፡
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ111 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዕቅዱን ለማሳካት በግብር ከፋዩ ዘንድ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት ለማስተካከል የተጠናከረ ትምህርታዊ ቅስቀሳና ክትትል እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በግብርና ዘርፍ በተሰማሩ ከ1 ሺህ 200 በላይ ባለሀብቶች ላይ የሚገኘውን ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ውዝፍ የግብር ገቢ ለማስከፈል እንደሚሠራም አስገንዝበዋል፡፡
ባለስልጣኑ በ2016 የበጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱንም ጠቅሰዋል፡፡