የሀገር ውስጥ ዜና

በጎዳና የሚኖሩ እናቶችና ልጆቻቸውን ለማንሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው

By Alemayehu Geremew

December 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎዳና የሚኖሩ እናቶች እና ልጆቻቸውን የማንሳት ፕሮጀክትን ለመደገፍ የገቢ ማሰባሰብና የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄ ሊካሄድ ነው፡፡

ንቅናቄው በሜሪጆይ የፕሮጀክት ባለቤትነትና በተሥፋ ኪነጥበብ ኢንተርፕራይዝ ፈፃሚነት የሚካሄድ ነው፡፡

ዛሬ በተሠጠው መግለጫ÷ መጪውን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ “በሊፍት (አሳንሰር) ከፍዬ እሳፈራለሁ በጎዳና የሚኖሩ ወገኖችንም አነሳለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ የገቢ ማሰባሰቢያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄው ይካሄዳል ተብሏል፡፡

ንቅናቄው ታኅሣሥ 22 ተጀምሮ ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል፡፡

ሊፍት ያላቸው ህንፃዎች ባለቤቶች፣ ተከራይ ድርጅቶች እንዲሁም ታዋቂ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ሐሳቡን እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል።

የሊፍት ወይም አሳንሰር ተጠቃሚዎች ተግባሩ የበጎ ሥራ መሆኑን በመረዳት አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ተጠይቋል።

የበጎ ሥራ ዘመቻው በቀጣዮቹ በዓላት እንደሚቀጥልም ነው የተመላከተው፡፡

በፍቅርተ ከበደ