Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

 

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሒደት ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ብዙ ተግባራትን ይጠይቃል ብለዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ ተቋሙን በግብአት እና በሰው ሀይል የማደራጀት፣ ወደ ተሀድሶ የሚገቡ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመለየት እና ከክልሎች ጋር በስራዎቹ ላይ መግባባት የሚፈጥሩ መድረኮች ማካሄዱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ ከ371 ሺህ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎች መኖራቸውን ጠቁመው መልሶ ወደ ማቋቋም ተግባር ከመገባቱ በፊት በድጋሚ የማጣራት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱና እንዲቋቋሙ የማድረጉ ስራ ከፍተኛ ሀብት እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

መንግሥት ለብሔራዊ ተሃድሶው ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀልና መልሶ የማቋቋም ስራ ለሀገሪቱ ልማትና ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ሚናው ቀላል እንዳልሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version