አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ማሊ እና ኒጀር ከፈረንሳይ ጋር ለረጅም ጊዜ የነበራቸውን የግብር ሥምምነት በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፥ ውሳኔው ፈረንሳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ ሀገራት የምታሳየውን ፀብ አጫሪ አመለካከት ተከትሎ የተወሰነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የግብር ሥምምነቱ ሚዛናዊነት የጎደለው እና በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የገቢ ኪሳራ የሚያስከትል በመሆኑ ለማቋረጥ መወሰናቸውንም ነው ወታደራዊ መሪዎቹ የገለጹት፡፡
ሀገራቱ በግብር ጉዳዮች ላይ ለትብብር እና አስተዳደራዊ እርዳታ ከፈረንሳይ ጋር የነበራቸው ሁለት ሥምምነቶች ማብቃቱንም አስታውቀዋል።
ኒጀር ከፈረንጆቹ 1965 ጀምሮ ከፈረንሳይ ጋር የገባችውን የግብር ሥምምነት ተግባራዊ ስታደርግ የቆየች ሲሆን፥ በተመሳሳይ ማሊ ከፈረንጆቹ 1972 ጀምሮ ከፈረንሳይ ጋር የገባችውን የግብር ሥምምነት ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ቀደም ሲል ቡርኪናፋሶ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የግብር ሥምምነት ያቋረጠች ሲሆን በአጠቃላይ የቀድሞ የፈረንሳይ ግዛት የነበሩት ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የግብር ስምምነታቸውን እንደሚያቋርጡ ቢቢሲ አፍሪካ ዘግቧል፡፡
ፈረንሳይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተደረሰ የቅኝ ግዛት ሥምምነት ከ14 የአፍሪካ ሀገራት ጋር የግብር ሥምምነት እንደነበራት መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሀገራቱ የወሰዱት እርምጃ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እንደሚያስችል ታምኖበታል።
ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በተቆጣጠሩ ወታደራዊ አንጃዎች እንደሚተዳደሩ ዘገባው አስታውሷል።